የባለስልጣኑ ኃላፊ መልእክት
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን በሳይንሳዊ እውቀት ላይ ተመስርቶ በክልሉ አካባቢን የሚጎዱና የሚበክሉ ተግባራትን በመከታተል፣ በመመርመር፣ በመቆጣጠርና የብዝሃ ህይዎት ሃብቶች መመናመንን በመከላከል የቀጣዩን ትውልድ የመወሠንና የመጠቀም መብት ሣይጋፉ በዘመኑ ላለው ትውልድ የተሻለ ጥቅም መስጠት የሚያስችል ዘላቂና ህጋዊ የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ሥርዓትን ማስፈንን ተልእኮው በማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ፣ የደንና የዱር እንስሳት ሃብትን በአግባቡ ለመጠበቅና ለማልማት ብሎም በእነዚህ ተግባራት ቅኝት በ2022 ለሰውና ለዱር እንስሳት መኖሪያ ምቹ የሆነ አካባቢ እንዲፈጠር ለመስራት የተቋቋመ ተቋም ነው።
ባለስልጣኑ ቀደም ሲል በአዋጅ 232/2008 ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 28 የሚደርሱ ዋና ዋና ተግባራትን መሠረት በማድረግ በአካባቢ፣ ደን እና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም የአማራ ክልል መንግስት የተቋሙን ተግባርና ኃላፊነት ማሻሻልና ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን በተቋማት መልሶ ማደራጀት ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 280/2014 መሰረት የተሰጠውን 39 ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በማድረግ ዘርፈ ብዙ የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ስለሆነም በክልሉም ሆነ በፌደራሉ መንግስት የተደነገጉ የአካባቢ ጥበቃና ደህንነት ህጎችን እና በሀገሪቱ የአካባቢ ፖሊሲ ውስጥ የሰፈሩ መሠረታዊ መርሆዎች ከግብ መድረሳቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በማስተባበር፣ በመንግስትም ሆነ በግል ኘሮጀክቶች (በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ የልማት ፖሊሲዎች፣ ስልቶች፣ ሕጎችና መርሃ – ግብሮች) ላይ የአካባቢና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማና የአካባቢ ክዋኔ ኦዲት ተግባራትን በማከናወን፣ ልዩ ልዩ የአካባቢ ህጎችንና መመረያዎችን በማውጣት፣ የአካባቢ ህጎች እንዲከበሩና ከብክለት ነጻ የሆነ ለመኖሪያ ምቹና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውንና እንደ ሀገር የተደረገውን አለማቀፋዊ ስምምነትም በክልላችን ተግባራዊ ለማድረግ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ በሆኑ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች የተፅዕኖዎች ማቃለያ እና መቋቋሚያ ስልቶች እንዲያከናውኑና እነዚህ ተግባሪ ተቋማት ይህንን ዘርፍ በመደበኛ እቅዳቸው አካተው በመተግባር የሚቀንሱትን የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መጠን ታሳቢ የሆነ ተግባር እንዲያከናውኑ በክትትልና ድጋፍ የማስተባበር እና የክልሉን የአካባቢ ሁኔታ ዘገባ በየወቅቱ እያዘጋጀ ለመንግስትም ሆነ ለህዝብ እንዲደርስና የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንዲቀመጡ ለማድረግ የተጀማመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
የተፈጥሮ ደኖችን፣ የብዝሃ ህይወት ሀብቶች መገኛ የሆኑ ብሔራዊ ፓርኮችና የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎችን በመጠበቅና በማልማት የአሁኑንና የመጭውን ትውልድ የመጠቀም መብት በማይጋፋ ሁኔታ በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖ*ሚን ከመገንባት ባሻገር የቱሪዝም ኢኮኖሚውን ለመገንባት ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡፡
በክልላችን የሚገኙ የተፈጥሮ ደኖችን በመንግስትና በህብረተሰቡ ቅንጅት እንዲጠበቁና እንዲለሙ በማድረግ፣ የተራቆቱ ተራራማ ቦታዎችን ከልሎ በማልማት፣ ከደን ሀብት ውጤቶች የሚሰበሰበውን የሮያሊቲ ክፍያ አፈፃፀም እንዲያድግ እና በዘርፉ ለክልሉ ወጣቶችና ሴቶች የሚፈጠረው የስራ እድል ፈጠራ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ እንዲሆን በየደረጃው ከሚገኘው መዋቅራችን፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የተቀናጀ ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ነገር ግን ከእነዚህ ውጤቶች ጎን ለጎን የሰው ልጅ ለህልውናው መሰረት የሆኑትን ህይወታዊና ህይወታዊ ያልሆኑ ቁሶችን የሚያገኝበትን አካባቢውን በቁጠባና በአግባቡ ባለመጠቀሙ እንዲሁም በምርት ሂደት የሚፈጠሩ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በአግባቡ ማስወገድ ባለመቻሉ ምክንያት በርካታ ችግሮች እየተከሰቱ፣ የተፈጥሮ ደኖች፣ ጥብቅ ስፍራዎችና ብሔራዊ ፓርኮች በህገ ወጦች ድንበራቸው እየተጣሰ ዛፎች እየተቆረጡ የዱር እንስሳት እየተሳደዱና ከፍተኛ ውድመት እየደረሰባቸው መሆኑ የጥበቃና ልማት ተግባሩን እየተፈታተነ ያለ ተግዳሮት ሆኗል፡፡
ችግሮቹ ከቀጠሉ ደግሞ የሰውን ልጅ በንጹህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብትን ጨምሮ በዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ፈተና በመሆናቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በየደረጃው ከሚገኘው የአካባቢ እና ደን ጥበቃ መዋቅራችን ጋር በአካባቢ ጥበቃ ተግባራት የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች ላይ በቅንጅት በመስራት እና የህዝብን ጥቅምና ደህንነት ወደ ጎን ትተው አካባቢን በሚበክሉና የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ተቋማት ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ በጋራ መረባረብ ይገባል፡፡
በመጨረሻም አካባቢን መጠበቅና ማልማት የሁሉንም አካላት ቅንጅታዊ እርብርብ የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን በመረዳት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የምትገኙ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎችን ጨምሮ መላው የክልላችንን የህብረተሰብ ክፍል፣ የሚመለከታችሁ የአስተዳደርና የህግ አካላት እንዲሁም በየደረጃው የምትገኙ የባለስልጣኑ አመራሮችና ባለሙያዎች የባለስልጣን መ/ቤታችንን ተግባርና ኃላፊነት መሠረት ያደረጉ ተግባራትን በማከናወን የሚጠበቅብንን ሚና እንድንወጣና ለቀጣዩ ትውልድ ምቹና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር እንድንሰራ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
ተስፋሁን አለምነህ
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ
ኢሜይል፡-alemnehtesfahun356@gmail.com
ፌስቡክ አድራሻ ፡- https://web.facebook.com/tesfahun2020
ባህርዳር ኢትዮጵያ
ለተጨማሪ መረጃዎች ሊንኮቹን በመጫን የባለስልጣኑ ኃላፊ በተለያዩ ጊዜዎች ከሚዲያዎች ጋር ያደረጉትን ቆይታ ይመልከቱ፡-
http://sharevideo1.com/v/bEtFc2x4eTBvc0k=?t=ytb&f=co
http://sharevideo1.com/v/OERDZS1rdHQ2YTQ=?t=ytb&f=co
https://www.facebook.com/share/r/18h2UKN2G7/
https://www.facebook.com/share/r/18j5wUWSSN/
https://www.facebook.com/reel/1336962516879062?mibextid=9drbnH&s=yWDuG2&fs=e
https://www.facebook.com/share/r/1Ez3b4PQs7/
https://www.facebook.com/reel/1715678615527438?mibextid=9drbnH&s=yWDuG2&fs=e