አካባቢ የሚለውን የአማርኛ ቃል የሚወክለው የእንግሊዘኛ ቃል “ኢንቫይሮመንት” ፍቺው ኢንቫይሮነር (Environner)ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል የተወሰደ ሲሆን በዙሪያችን የሚገኙ ነገሮችን ያጠቃለለ ማለት ነው፡፡ ይህም በቁሳዊው ዓለም ውስጥ ያሉትን በዙሪያችን የሚገኙ ነገሮችን እንደ አፈር፣ ውኃ፣ አየር፣ የሰው ልጅ፣ እፅዋት፣ እንስሳት፣ አነስተኛ ነፍሳትና ሌሎችንም ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ቀስ በቀስም አካባቢ ለሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም በመስጠት ሰዎችን ጨምሮ ሌሎች ሕይዎት ያላቸው ነገሮች ከቁሳዊው ዓለም ጋር ያላቸው ተራክቦ ወይም ግንኙነት እንዲጨምር ተደረገ፡፡ ከዚያም ሁኔታዎች እየተሻሻሉና ዕድገት እየተፋጠነ ሲሄድ ፍቺው ወይም ትርጉሙም በዚያው ልክ እየሰፋ የሰው ልጅ በሚያደርጋቸው የማህበራዊ፣ ባህላዊና የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች ከአካባቢ ጋር ቁርኝት እንዳላቸው በማረጋገጥ እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች እንዲያካትት ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት የሰው ልጅ የሚገነባቸው ግንባታዎች፣ ቁሳቁስ፣ እናቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ሁሉ በዚህ ትርጉም ውስጥ ተካትተዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ አካባቢ የሚለው ቃል ሕይዎት ያላቸውን እና ሕይዎት የሌላቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያጠቃልል ሆኗል፡፡ የኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ልማት ዕድገት በማህበረሰቡ የማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታዎች ላይ ተፅዕኖስለሚያሳድር አካባቢ የሚለው ቃል ሰፋ ያለ እይታ እንዲኖረው በማድረግ ማናቸውንም በዓለማችን ያሉ ነገሮችንና በመካከላቸው ያለውን ተራክቦ ወይም ግንኙነት ሁሉ ይዟል፡፡
ዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ሕግ (1986 እ.ኤ.አ) አካባቢ የሚለውን ቃል የአፈር፣ ውኃ፣ አየር፣ መሬትና እነዚህ ሁሉ ከሰው ልጅ ጋርም ሆነ ሌሎች ህይዎት ካላቸው ነገሮች ጋር ያላቸውን ቁርኝት ያካተተ ነው በሚል ይገልፀዋል፡፡ በዙሪያችን የሚገኙ አፈር፣ አየር፣ ውኃና ሌሎችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሰው ልጅ ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ የሰው ልጅ በራሱም ቢሆን በአካባቢያ ላይ በሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ (የተፈጥሮ ሀብቶቻችን አለአግባብ ወይም ከመጠን ባለፈ በመጠቀም)፣ በአካባቢ ላይ በሚያደርሰው ብክለት እና በእንስሳትም ሆነ በዕፅዋት ላይ በሚኖር የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚደርሱ ተፅዕኖዎች ምክንያት የሚፈጠር ችግር አለ፡፡ በመሆኑም ከላይየተዘረዘረው ጥቅል ድምር ውጤት አካባቢ የሚል ስያሜ አግኝቷል፡፡
ሕይዎት ያላቸውና ሕይዎት የሌላቸው ነገሮች ከአካባቢ ጋር ያላቸው መስተጋብር
የከተማና የገጠር የአካባቢ ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ በከተማ ውስጥ ከፍተኛ የአካባቢ ጫና አለ፡፡ በትላልቅ የመኖሪያና የድርጅት ህንጻዎች ግንባታ፣ የፋብሪካዎችና የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ የመንገድ አውታሮች መዘርጋት፣ በአፈር፣ በውኃና በአየር ብክለት ከፍተኛ ጉዳት ይከተላል፡፡ ከመፀዳጃ ቤቶች፣ ከፋብሪካ የፍሳሽ ልቀት፣ ከደረቅ ቆሻሻ መብዛት ምክንያት ከፍተኛ የአካባቢ ብክለት ይደርሳል፡፡ በከተሞች ውስጥ ከፍተኛ የድምፅ ብክለት ችግር ይከሰታል፡፡ በገጠር የሚደርሰው የአካባቢ ጉዳት ከከተማው የተለየ ነው፡፡ በአብዛኛው አፈር በጎርፍ መታጠብ፣ በልቅ ግጦሽ፣ በኋላ ቀር አስተራረስ፣ በደን ጭፍጨፋ ምክንያት የአካባቢ መጎሳቆል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለአዝዕርት ምርት ዕድገት ይረዳሉ የተባሉ የተባይ መከላከያ መድኃኒቶች፣ ዘመናዊ የአፈር መዳበሪያ፣ የአረም መከላከያ መድኃኒቶች ምክንያት የገጠሩ አካባቢ የአየር፣ የውኃና የአፈር ብክለት ይደርስበታል፡፡
የአካባቢ ጥናት ወሰን
የአካባቢ ጥናት እንደ አንድ የትምህርት ክፍል ስናየው በርካታ ነገሮችን ይይዛል፡፡ በርካታ ጉዳዮችንና ክፍሎችንም ይሸፍናል፡፡ ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ደግሞ የሚከተሉትን ዋና ዋና ፍሬ ሃሳቦች እናገኛለን፡፡
የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅና አጠቃቀም
ስነ ምህዳርና ብዝሃ ሕይዎት
የአካባቢ ብክለትና ቁጥጥር
ከአካባቢና ልማት ጋር የተገናኙ የማህበራዊ ነክ ጉዳዮች
የስነ ሕዝብና የአካባቢ ነክ ጉዳዮችን ይሸፍናል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ከማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ጋር ቀጥተኛ ጥቅም ያላቸው የአካባቢ ጥናት መሰረታዊ ጉዳዮችናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢ ጥናት በልዩ ዘርፍ የሚታዩ እንደ የአካባቢ ሳይንስ፣ የአካባቢ ምህንድስና ወይም የአካባቢ አያያዝን የመሳሰሉ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ይይዛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአካባቢ ጥናት ወሰን (ሽፋን)በፍጥነት እያደገ መላውን ዓለም አዳርሷል፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያዩ ተጨማሪ ዘርፎች ወይም መስኮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በአካባቢ ላይ የሚደረግ ምርምርና ልማት፣
የአረንጓዴ አካባቢ ተሟጋች፣
የአረንጓዴ ግብይት፣
አረንጓዴ የብዙኃን መገናኛ፣ ድንቅ ተፈጥሮ የራድዮ ፕሮግራም
የአካባቢ አማካሪ እና የመሳሰሉት እየተስፋፉ ነው፡፡
የአካባቢ ጠቀሜታ ምንድን ነው?
አካባቢ ሁሉንም የሚሸፍንና ለሁሉም ጠቃሚ ነው፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ በየትኛውም ስራ ይሁን የዕድሜ ደረጃ ላይ ያለ ሰው ሁሉ በሚሰራው ሥራ በአካባቢ ላይ ጉዳት ያደርሳል፣ እንደገናም በአካባቢ ላይ በሚደርስ ጉዳት ተጠቂ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ በዓለማችን ላይ አካባቢን መሰረት ያደረጉ ዓለማቀፍ የአካባቢ በዓላት ይከበራሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉትን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ሰንጠረዢ 1፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበሩ የአካባቢ በዓላት ቀን
ተ.ቁ የሚከበረው በዓል በየዓመቱ የሚከበርበት/የሚታሰብበት ጊዜ
1 የአየር ንጣፍ ሳምንት መስከረም 5-12
2 ከመኪና ነጻ ቀን መስከረም 11 ቀን
3 የአረንጓዴ ሸማቾች ቀን መስከረም 12 ቀን
4 የዓለም የእርሻ እንስሳት ቀን መስከረም 23 ቀን
5 የዓለም የመኖሪያ ስፍራ ቀን መስከረም 24 ቀን
6 የዓለም የእንስሳት ደህንነት ቀን መስከረም 25 ቀን
7 ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ አደጋ ቅነሳ በዓል ጥቅምት 5 ቀን
8 የተፈጥሮ ጥበቃ ቀን ጥቅምት 16 ቀን
9 የፅዳት ቀን ህዳር 9 ቀን
10 የዱር እንስሳት ሳምንት ህዳር 22-28 ቀን
11 ዓለም አቀፍ የስነ ሕይዎት ብዝሃነት ቀን ታህሳስ 21 ቀን
12 የዓለም ውኃ አዘል መሬት ቀን ጥር 24 ቀን
13 የአፍሪካ የአካባቢ ቀን የካቲት 24 ቀን
14 የዓለም የደን ቀን መጋቢት 13 ቀን
15 የዓለም የውኃ ቀን መጋቢት 14 ቀን
16 የዓለም የአየር ንብረት ቀን መጋቢት 15 ቀን
17 የዓለም የወንዞች ቀን መጋቢት 16 ቀን
18 የመሬት ቀን ሚያዚያ 14 ቀን
19 የዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይዎት ቀን ግንቦት 14 ቀን
20 ፀረ ሲጋራ ቀን ግንቦት 24 ቀን
21 የዓለም የአካባቢ በዓል ቀን ግንቦት 28 ቀን
22 የዓለም ሀይቆች ቀን ሰኔ 1 ቀን
23 የዓለም የስነ ሕዝብ ቀን ሰኔ 4 ቀን
24 የዓለም በርሃማነት መስፋፋትን መከላከል ቀን ሰኔ 10 ቀን
25 የዓለም የዛፎች ቀን ሐምሌ 3 ቀን
አንባቢያን ለመሆኑ ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ዓለም አቀፍ የአካባቢ በዓላት ቀን በአገራችን የትኞቹ ይከበሩ ይሆን?
አካባቢ ዓለማቀፋዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ እንደ የዓለም ሙቀት መጨመር፣ በዓለም ከመጠን ያለፈ ቅዝቃዜ፣ የአየር ንጣፍ መሳሳት፣ የደንና የሀይል አቅርቦት መቀነስ፣ የዓለም የብዝሃ ሕይዎት መመናመንና የመሳሰሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰውንልጅ በአጠቃላይ የሚጎዱ ቢሆንም ችግሮቹን ለመከላከል ዓለማቀፋዊ ዕቅድ እንዲታቀድና ሰፊ ስራ በጋራ መውሰድ እንዲቻል ያሳስባሉ፡፡ ከዚህ ሌላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይሆን በአንድ አካባቢ ብቻ የሚወሰኑ አገር አቀፍ፣ ክልል አቀፍ ወይም በውሱን ቦታ ብቻ የሚከሰቱ የአካባቢ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የማዕድንና የኤሌክትሪክ መብራት ፕሮጄክቶች ግንባታ የሚደርሱ አሉታዊ ተፅዕኖዎች፣ የአካባቢ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የወንዞችና ሀይቆች ብክለት፣ የአፈር መከላት፣ የውኃ መተኛትና የጨዋማነት መከሰት፣ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል እንደየአካባቢው ሁኔታ ይታሰባል፣ ይከናወናል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ህብረተሰቡን የማስተማር፣ የማሳወቅና የመቀስቀስ ስራዎች በየደረጃው በስፋት ይተገበራሉ፡፡
ሁለተኛው በግለሰቦች ደረጃ የሚኖረው የአካባቢ ጠቀሜታ ነው፡፡ በሰዎች ላይ የሚደርሱ አካባቢያዊ ችግሮች ሁሉንም ግለሰብ የሚነኩ ከፍተኛ ችግሮች እንደመሆናቸው መጠን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የአካባቢ ጥናት ማካሄድ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ መልክ ከሚደርሱት ችግሮች ውስጥ ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት አለመኖር፣ ንፁህና ለጤና ተስማሚ የሆነ አየር ማጣት፣ የመሬት ለምነት መጥፋት፣ ለጤና ተስማሚ የሆነ የምግብ ዕጥረትና በዘላቂነት አለማግኘት፣ የድምፅ ብክለትና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ማንም ሰው በንፁህና ጤናማ ፣ ለዕይታና ለኑሮ ተስማሚ አካባቢ መኖር ከፈለገ፣ ንፁህና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ለረጅም ጊዜ እንዲኖረው ከተመኘ፣ እነዚህን ሁሉ ደግሞ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለመጭው ትውልድም መኖር እንዳለበት ካወቀ የአካባቢን መሰረታዊ ጉዳዮች መረዳት አለበት፡፡ ስለሆነም የሰው ልጅ በአካባቢ ጥናት ላይ ተመስርቶ ዕውቀቱን፣ አስተሳሰቡን፣ አስተያየቱንና ግንዛቤውን በአካባቢ ትምህርት በየጊዜው እያጎለበተ ወደ አካባቢ እንክብካቤ ተግባራት ከተሰማራ ችግሮቹን መቀነስ ይችላል፤ ያሰበውንም ይፈጽማል፡፡እንደ አካባቢ ምሁራን አገላለጽ ጥሩ አካባቢ ከሌለህ ቆንጆ ቤት ቢኖርህ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ አካባቢው አንተን ይበክልሃል ይባላልና፡፡
ስለሆነም ህብረተሰቡን ስለ አካባቢ ጠቀሜታ ማስገንዘብ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም፦
• አካባቢ ለሁሉም ስለሆነ አጠቃላይ ህብረተሰቡ የሚሳተፍበት የአካባቢ አያያዝ ዕቅድና አፈጻጸም ግዴታ መሆኑን ማስገንዘብ ማስፈለጉ፣
• የሰው አኗኗርና የሚጠቀምበት ቴክኖሎጂ ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሄድ ሁሉም ለራሱ ብቻ ማሰብና ስለሌላው አለመጨነቅን ስለሚያሳይ አካባቢ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እምብዛም ላያሳስበው ይችላል፡፡ ሰለዚህ እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብና አመለካከት መቀየር የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠር ጠቃሚ በመሆኑ፣
• የሰው ልጅ ንፁህና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው አውቆ በጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የአካባቢ ችግሮችን በጋራ እንዲከላከል ማስተማር እና
• የአካባቢ ችግሮችን በመለየት ችግር ፈቺ ዕቅዶችን በጋራ በማቅድ ለጊዜያዊ ሳይሆን ለዘለቄታዊ ልማትና ዕድገት የሚያገለግሉ የልማት ተግባራትን በማከናወን የመጭውን ትውልድ ደህንነት ማስጠበቅ እንዳለብን በስፋት ህብረተሰቡን በአካባቢ ትምህርት ማስገንዘብ፣ ማሳወቅ፣ የአመለካካት ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግና በእነዚህ ተጠቅሞ በአካባቢ ልማት እንዲሳተፍ ማድረግ በማስፈለጉ ነው፡፡
የልምድ ልውውጥ አንዱ የግንዛቤ መፍጠሪያ ተግባር ነው
በአካባቢ ላይ ከሚከሰቱ ዋና ዋና ተፅዕኖዎች
በአካባቢ ላይ የሚደርሱ ዋና ዋና ተፅዕኖዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ከግብርና ልማት ጋር የተያያዙ ተፅዕኖዎች፦ ይህ በሁለት ተከፍሎ ይታያል፡፡ የዘመናዊ እና ኋላቀር የግብርና ስራዎች ሲሆኑ በዘመናዊው ግብርና ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የሚረዱ ከምርጥ ዘር፣ ከፀረ-ተባይ፣ ከዘመናዊ የመሬት ማዳበሪያ አጠቃቀም፣ ከውኃ መተኛትና ከአፈር ጨዋማነት የተያያዙ ተፅዕኖዎች የሚከሰቱ ሲሆን በኋላቀር አስተራረስ ምክንያት ደግሞ የደን መጨፍጨፍ፣ የአፈር መከላትና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች መቀነስና መሰልጉዳቶች ይከሰታሉ፡፡
በልቅ ግጦሽ ምክንያት በአካባቢ ላይ ጉዳት ይደርሳል
2. ከቤት ልማት ጋር የተያያዙ ተፅዕኖዎች፦ ከቤት ልማቱና ከዚሁ ጋር ተያያዢነት ካላቸው የኃይል አጠቃቀም ችግሮች፣ በግንባታው ምክንያት የሚደርሱ የመሬት መጎሳቆሎችና የለም አፈር መመናመን፣ ለልማቱ ከታሰበው ቦታ ላይ የሚጨፈጨፉ ደኖችና በዚህም ሰበብ የተፈጥሮ ሀብቶችና ብዝሃ ሕይዎት መመናመን፣ መርዛማነት ያላቸው ልቀቶች በጤና ላይ የሚያደርሱት ጉዳት፣ በስራ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችና ሌሎችም ይካተታሉ፡፡
3. ከማዕድን ማምረት ሥራ ጋር የሚደርሱ ተፅዕኖዎች፦ በዚህ ምክንያት በስነ ምህዳር ላይ፣ በማህበራዊ ምጣኔ ሀብት ጉዳቶች፣ የአካባቢ ብክለት፣ ከስራው ጋር ተያያዢነት ያላቸው ተፅዕኖዎች እና በስራ ቦታው ላይ የሚደርሱ አካላዊ ተፅዕኖዎች ይጠቃለላሉ፡፡
4. ከኢንዱስትሪ ልማትና መስፋፋት ጋር የተያያዙ ተፅዕኖዎች፦ የውኃ፣ የአየርና የአፈር ብክለቶች፣ የመሬት መጎሳቆል፣ የደን መመናመንና በስራ ላይ የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
5. ከትራንስፖርት ጋር የተያያዙ ተፅዕኖዎች፦ ለመንገድ አውታር ሲባል በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ የድምፅና የአየር ብክለት፣ ከስራ ጋር ተያያዢነት ያላቸው ተፅዕኖዎች ይከሰታሉ፡፡
ከላይ በተገለጹት ዋና ዋና የአካባቢ ተፅዕኖዎች ምክንያት የአካባቢ ብክለት አንዱ የአካባቢ ችግር ይሆናል፡፡ በአካባቢ ብክለት ስር የሚጠቃለሉት ደግሞ የውኃ ከመሬት በላይና ከመሬት ውስጥ ያሉ የውኃ አካላት፣ የአፈር ወይም የመሬት መበከል፣ የአየር ብክለት (ተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚደርስ ብክለት)፣ የድምፅ ብክለት (ተንቀሳቃሽ ከሆኑና ከማይንቀሳቀሱ ነገሮች የሚለቀቅ ድምፅ)፣ ናቸው፡፡ በእነዚህ የአካባቢ ብክለቶች ምክንያት የአየር ንብረት መለወጥና የዓለም የሙቀት መጠን እየጨመረ እንደሄደ ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለሰው ልጅም ሆነ ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ ከፍተኛ ችግርን በማስከተል ላይ ነው፡፡
በአያያዝ ጉድለት የተጎዱ መሬቶችን መልሶ ማገገም ከአካባቢ ጥፋት ያድናል
በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?
የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመርን መከላከል (የሕዝብ ቁጥር መጨመር አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን አገራት የሕዝብ ቁጥር ዕድገታቸው ከምጣኔ ሀብታቸው ዕድገት ጋር የተመጣጠነ ካልሆነና በፍጥነት እየጨመረ ከሄደ መከላከል አለባቸው)፡፡
የተፈጥሮ ሀብቶቻችን መጠበቅና በአግባቡጥቅም ላይ ማዋል (ታደሽና ታዳሽ ያልሆኑ ሀብቶችን መለየትና በጥንቃቄ መጠቀም)
የኃይል አጠቃቀማችን ማስተካከል
በአካባቢ ላይ የሚደርሱ ብክለቶችንና ብክነቶችን መከላከል
የአካባቢ ትምህርትን በስፋትና በጥልቀት ለህብረተሰቡ ማስረጽ
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ምጣኔ ሀብት መገንባት
የዓለም ሙቀት መጨመርን መከላከል (የዓለም ሙቀት መጨመር ከፍ እንዳይል መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች የሚከተሉት ናቸው)፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለውን የክሎሮፍሎሮ ካርቦንና ነዳጅ አጠቃቀም መጠንን መቀነስ
የኃይል አጠቃቀማችን በአግባቡ መጠቀም
ታዳሽ ኃይሎችን መጠቀም
የኑክሌር ኃይልን ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዋል
የደንጋይ ከሰል ከመጠቀም ወደ ተፈጥሮ ጋዝ መሸጋገር
ሜቴንን ለኃይል ጥቅም ማዋል
የቤት እንስሳት ቁጥርን መቀነስ
ብዙ ዛፎችን መትከል
የተቃጠለ አየርን በአግባቡ ማስወገድ
ዘላቂ የግብርና ልማት መጠቀምና ሌሎችም
ምንጭ
1. National Center for Education Statistics. Classification of Instructional Programs (CIP 2000)-(03) NATURAL RESOURCES AND CONSERVATION. Institute of Education Sciences,United States Department of Education. [Accessed 29 January 2010]
2. http://www.esf.edu/es/history.htm
3. http://www.middlebury.edu/academics/es
4. http://www.esac.ca/about/a-brief-history-of-esac/ “A Brief History of ESAC”. Accessed 12 March 2012.
የእኛ ራዕይ
የእኛ ራዕይ:
የአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነትን በማረጋገጥ፣ የደንና የዱር እንስሳት ሃብትን በአግባቡ በመጠበቅና በማልማት፣ በ2017 ለሰውና ለዱር እንስሳት መኖሪያ ምቹ የሆነ አካባቢ ተፈጥሮ ማየት፤
ተልእኳችን
በሳይንሳዊ እውቀት ላይ ተመስርቶ በክልሉ አካባቢን የሚጎዱና የሚበክሉ ተግባራትን በመከታተል፣ በመመርመርና በመቆጣጠር፣ የብዝሃ ህይዎት ሃብት መመናመንን በመከላከል የቀጣዩን ትውልድ የመወሠንና የመጠቀም መብት ሣይጋፋ በዘመኑ ላለው ትውልድ የተሻለ ጥቅም መስጠት የሚያስችል ዘላቂና ህጋዊ የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ሥርዓትን ማስፈን፡፡
እሴቶች
- የአካባቢ ደህንነትና ዘላቂነትን ማረጋገጥ፣
- የህብረተሰብ ተጠቃሚነት፣
- የብዝሀ ህይዎት ሃብትን መንከባከብ፣
- ለለውጥ ዝግጁነት፣ የሙያ ፍቅር፣
- ታታሪነትና ውጤታማነት፣
- የላቀ አገልግሎት፣
- አሳታፊነት፣
- የህግ የበላይነት