በአማራ ክልል የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች የሚተገበሩትና የሚተዳደሩት በኢፌዲሪ የዱር እንስሳት ልማት ፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 544/1999 ፤ እንዲሁም የዱር እንስሳት ልማት ፣ ጥበቃና አጠቃቀም ደንብ ቁጥር 163/2001 እና ሌሎች በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት ደረጃ በአሁን ወቅት ተፈጻሚነት ባላቸዉ ህጎች መሰረት ነዉ፡፡
ሆኖም በዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ስር ወደ ሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት እና ወደ ተለያዩ ውጤቶች ከመግባታችን በፊት አንባቢው በርእሱ ዙሪያ ያሉትን አንዳንድ ውሎችን እና ፅንሰ፡ሀሳቦችን መረዳቱ ጠቃሚ ነው፡፡ የሚከተሉትን ቃላት በዱር እንስሳት ልማት ፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 541/1999 መሠረት መግለጽ በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡
የዱር እንስሳት ማለት ከቤት እንስሳት በስተቀር ማንኛውም በሂወት ያለ ወይም የሞተ የጀርባ አጥንት ያለዉ ወይም የሌለዉ እንስሳ ማለት ነው፡፡
የዱር እንስሳት ሀብት ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳት ማለት ሲሆን ከሀገር ወደ ሀገር የሚሰደዱ እና ለጊዜዊነት በኢትዮጵያ የሚቆዩትን ዝርያዎች ያጠቃልላል፡፡
የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታ ማለት ለዱር እንስሳት ጥበቃ ተብሎ የተከለለ አካባቢ ሲሆን ብሔራዊ የዱር እንስሳት ጥበቃ ፓርኮችን ፣ የዱር እንስሳት መጠለያዎችን ፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ ክልሎችን እና በዱር እንስሳት የቁጥጥር አደን ቦታዎችን ያጠቃልላል፡፡
ብሔራዊ ፓርክ ማለት የዱር እንስሳትን እና ከነዚሁ ጋር የተያያዙትን ሐይቆችን እና ሌሎች በውሃ የተሸፈኑ ስፍራዎችን ጨምሮ ለአካባቢዉ ዉበትና ለሳይንሳዊ እዉቀት የሚረዱትን የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅ የሚከለል ቦታ ነው፡፡
የዱር እንስሳት ሀብትን የመጠበቅና ማልማት ተግባር በአብክመ አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ውስጥ በዱር እንስሳት ጥበቃ፣ ልማትና አጠቃቀም ዋና የሥራ ሂደት ካሉት ዋና ዋና ሥራዎች አንዱ ነው፡፡ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ሥራ ውጤት በአንዳንድ የተገለጹ የፖሊሲ ግቦች ስር በተለያዩ ክፍሎች የሚፈጸሙ ንኡስ ተግባራት እና ስትራተጂዎች ድምር ዉጤት ነዉ። ከነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸዉ።
ብሔራዊ ፓርኮችና ሌሎች ጥብቅ ስፍራወች ህጋዊ ሰውነት ኖሯቸው ዓለም አቀፍ መርሆወችንና ደረጃወችን ጠብቀው እንዲተዳደሩ ማድረግ በዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ስር አንዱ አላማ ሲሆን ለማሳካት የሚከተሉት ስትራትጂዎች ትግባራዊ ይደረጋሉ።
- ጥብቅ ስፍራወችን ማቋቋምና ሕጋዊ ማድረግ
- ለጥብቅ ሥፍራወች ማኔጅመንት ፕላን ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ
- በዱር እንስሳት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የልማት እንቅስቃሴወችን መቀነስ
- የአስተዳደሩንና ማኔጅመንት ፕላኑን ተግባራዊ ለማድረግ አዋጅ፣ደንብና መመሪያ ማዘጋጀት
በሌላ በኩል ከጥብቅ ቦታወች ውጭ ያሉ የዱር እንስሳት በአግባቡ እንዲተዳደሩና እንዲጠበቁ ማድረግ ክዚህ ዘርፍ የሚጠበቅ ሲሆን ይሄን ለማሳካት የተለያዩ ሰልቶችና ተግባራት ይከናወናሉ።
- እንደአስፈላጊነቱ በማጥናት ወደ ጥብቅ ቦታነት ማሳደግ
- ከጥብቅ ቦታወች ውጭ ያሉ የዱር እንስሳት የሚተዳደሩበትን ደንብና መመሪያ ስራ ላይ ማዋል
- ህብረተሰቡ ከጥብቅ ቦታወች ውጭ ያሉ የዱር እንስሳትን በባለቤትነት ይዞ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ
በሀገሪቱ ውስጥ ብቻና በእልቂት ስጋት ላይ ለሚገኙ የዱር እንስሳት ልዩ ጥበቃ ማድረግ በዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ የስራ ሂደት ዉስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠዉ ጉዳይ ሲሆን ይህን ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ስትራተጂዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ።
- በሀገራችን ብቻ የሚገኙ እንስሳት እንዲጠኑና በዘቦታ እንዲጠበቁ ማድረግ
- በመጥፋት ላይ ለሚገኙ እንስሳት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ማስወገድ
- በእልቂት ስጋት ላይ ያሉ እንስሳትን ወደምቹ ቦታወች እንዲዛወሩ/የኢዘቦታ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ሁኔታወችን ማመቻቸት
ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ የሚከተሉትን የፖሊሲ ግቦች ማሳካት አስፈላጊ ነው፡፡
- የዱር እንስሳትን ከልዩ ልዩ አደጋወች ለመከላከል የሚያስችል የጥበቃ ስርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ
- በጥብቅ ቦታወችና ውጭ በሚገኙ የዱር እንስሳት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ በሽታወችን ለመከላከል የሚያስችል ስርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ
- የዱር እንስሳትንና ውጤቶቻቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት