የዱር እንስሳት የሚሰጡትን ጥቅም በመለየት በዘላቂነት ለጥቅም እንዲውሉ ማድረግ በዱር እንስሳት ልማት ፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዋና የስራ ሂደት ስር ትኩረት የሚሰጠዉ ዋና ተግባር ነዉ። ይህን ለማሳካት በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል መረጃ ለማግኘት ቆጠራ ማካሄድ፤ በቁጥጥር አደን ቀበሌና ከጥብቅ ቦታወች ውጭ ስፖርታዊ አደንን ተግባራዊ ማድረግ እና፤ ወቅታዊ መረጃ ማደራጀትና ለተጠቃሚወች ማድረስ እንደ ስትራተጂ የምንከተላቸው ናቸው።
ሌላዉ በዱር እንስሳት አጠቃቀም ዉስጥ የተፈጥሮ አካባቢንና እንስሳትን በማይጎዳ ሁኔታ በጥብቅ ስፍራወች ውስጥ የኢኮ-ቱሪዝም እንቅስቃሴ ማድረግ በአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የዱር እንስሳት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዋና የስራ ሂደት እንደ ቁልፍ ተግባር የሚውሰድ ነዉ። ለዚህም መሳካት ኢኮ-ቱሪዝም እንዲስፋፋ ስርዓት መዘርጋት፤ መሰረተ፡ ልማቶችን ማስፋፋትና፤ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ደንቦችንና መመሪያዎችን ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ የሚተገበሩ ስራዎች ናቸዉ።
ከዱር እንስሳት ሀብት የሚገኘዉን ገቢ በተመለከተ ገቢው ለአካባቢው ህብረተሰብ፣ ለልማት ጥበቃና ለኢኮኖሚ እድገት እንዲውል ክትትል ማድረግ በዱር እንስሳት ሀብት አጠቃቀም ዋና ተግባር ዉስጥ የሚካተት ነዉ። በተጨማሪም ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሳተፉ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።