የደን ዘርፍ የክልሉን እና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲያበረክት የሚፈለግ ከሆነ የደን ልማት ፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም በአግባቡ እና በዝርዝር መመሪያዎችን እና ደንቦችን በመጠቀም መተዳደር አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአካባቢ ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ለባለስልጣኑ ማቋቋሚያ ወጣው አዋጅ ላይ (አዋጅ ቁጥር 232/2015) እንደተገለጸው ለክልሉ ዘላቂ የደን ልማት ፣ ጥበቃና አጠቃቀም መመሪያዎችን የማውጣት ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
ስለሆነም የአደዱጥልባ የተፈጥሮ ደኖች ጥበቃና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የሚከተሉትን ዋና ዋና ኃላፊነቶች አሉት፡፡
የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ህጎችን በክልሉ ውስጥ ተፈፃሚ ለማድረግ የሚያስፈልጉትን መመሪያዎች ያወጣል፣ ተግባር ላይ እንዲውል ያደርጋል፣
በአሁኑ ወቅት የኢፌዴሪ የደን ልማት ፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1065/2010 በክልሉ የደን ልማት ፣ ጥበቃና አጠቃቀምን ተግባራዊ ለማድረግ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ እንደተገለጸው የደን ልማት ፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 542/1999 በአዲሱ ተሽሯል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በወጣው አዋጅ መሠረት በክልል እና በፌዴራል መንግሥት የወጡ ሕጎች ፣ ደንቦችና መመሪያዎች ከአዲሱ አዋጅ ጋር የማይጣጣሙ በመሆናቸው ሊተገበሩ እንደማይችሉ ተብራርቷል፡
ይህንንም ተከትሎ የአደዱጥልባ የተፈጥሮ ደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የደን ልማት ፣ ጥበቃ ፣ አጠቃቀምና ቁጥጥር ዝርዝር መመሪያ አዘጋጅቷል (መመሪያ ቁጥር 002/2010)፡፡ በክልሉ ምክር ቤት የፀደቀው መመርያው በክልሉ ለሚገኙ ዞኖች ተላልፎ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡